Monday, 18 August 2014



  የውህደቱ ዓላማዎች
                                                             
                                                             አስራት አብርሃም

ተዋሃደ፣ አንድ ሆነ እንዲል መፅሐፉ፤ የአንድነትና የመኢአድ አባላት ዘመኑን በውህደት የሚጀምሩበትና አንድ የሚሆኑበት ቀን ላይ ደርሷል። በዚህም ምክንያትም አዲስ ፓርቲ፣ አዲስ ፕሮግራም እና አዲስ መሪ ይኖረን ዘንድ መልካም ፍቃዳቸው ሆኗል። ይህ ውህደት የጋራ ቤታችን ለሆነችው ለውዲቷ ሀገራችን ያለንን በጎ ምኞትና ሀሳብ የምንገልፅበት፤ እንደህዝብ ያሉንን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች መልሰን የምናስተሳስርበት መልካም አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ። ውህደት ሲባል በተለያዩ ፓርቲዎች ውስጥ የነበሩትን አባላት ወደ አንድ ፓርቲ ማምጣት ማለት አይደለም፤ ሰዎች አይደለም እየተዋሃዱ ያሉት፤ እየተዋሃደ ያለው ሀገራዊ ዓላማ ራዕይ ነው። ለዚህ ሀገራዊ ዓላማና ራዕይ ሲባል ነው ሁለት የነበሩ ፓርቲዎች አንድ የሚሆኑት። በዚህ ምክንያት ደግሞ የፓርቲ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ሀገር ነው የሚወሃደው፤ ኢትዮጵያውያን ናቸው በዜግነት ላይ በተመሰረተ የእኩልነትና የነፃነት መርህ የሚዋሃዱት።
ለመግቢያ ያህል እህን ካልኩኝ ለመሆኑ የውህደቱ መሰረታዊ አላማዎች ምንድናቸው? በሚለው ጉዳይ ላይ የተወሰነ ነገር ለማለት እፈልጋለሁ። ውህደቱ በዋናነት የተፈለገው ሁለቱም ፓርቲዎች በተናጥል ሊያሳኩት ያልቻሉትን ፖለቲካዊ ዓላማ አንድ ላይ ሆኖ ለማሳካትና ከግብ ለማድረስ በማሳብ ነው። ይህ ደግሞ በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን ያለመታማመን መንፈስ ይህ ውህደት ምሳሌ በመሆን አብሮ አንድ ላይ ሆኖ እንዴት የተሻለ ነገር መስራት እንደሚቻል ለማሳየት ተነሳሽነቱ የመውሰድ ነገር ነው።በዚህም ምክንያት ይህ ውህደት የመጀመርያ እንዳልሆነ ሁሉ የመመጨረሻም አይሁንም ከአሀሁን በፊትም አንድነትና ብርሃን ያደረጉት ውህደት ብዙ ባይነገርለትም እጅግ በጣም የተሳካ እንደነበር መረዳት የሚቻል ነው። በቀጣይነትም በመድረክ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችና ሰማያዊዎች የዚህ ትልቅ ሀገራዊ የሆነ ፖለቲካዊ አቅም የመፍጠር ፕሮጀክት አካል ይሆናሉ ብዬ ነው የማስበው።
ዘላቂ የሆነ ፖለቲካዊ ለውጥ ማምጣት የምንችለው እውነተኛ የዴሞክራሲና የለውጥ ኃይሎች የሆኑትን ወደ አንድ የተጠናከረና የተደራጀ ኃይልነት መሸጋገር ሲችሉ ነው፤ ውድድሩም የሁለትዮሽ ብቻ ነው መሆን አለበት፤ በኢህአዴግና በአንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ እንደሚሉት በአውራ ገዥ ፓርቲና በዴሞክራሲያዊ አውራ ፓርቲ መካከል ነው መሆን ያለበት። ከዚህ ውጪ ያሉት ሌሎች ፓርቲዎች በክልልና በከተሞች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ለምሳሌ የክልል ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ አዲስ አበባና ድሬዳዋ የራሳቸው የሆኑ የከተማ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ሊኖራው ይችላል፤ ሀገራዊ የሆኑ ፓርቲዎች ግን ወደ አንድ ጠንካራና ዘላቂ ኃይል መሰባሰብ መቻል አለባቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊው አውራ ፓርቲ ራሱን የቻለ ነፃነትና ያልተማከለ ስልጣን ያለው የክልልና የከተማ መዋቅር ይኖረው ዘንድ የተገባ ነው። በዚህ መንገድ ነው ከክልሎችም ሆነ ከከተማ ፓርቲዎች የተሻለ ሰፊ መዋቅርና ተደማጭነት እንዲኖረው የሚሆነው። ቀስ በቀስ ወደ ተረጋጋና ዘላቂነት ወዳለው ፖለቲካዊና ሀገራዊ ሁኔታ ለመምጣት ወደ ሁለት ፓርቲ ስርዓት መምጣት መቻል አለብን። ለዚህ ደግሞ ልዩ ልዩ ፍላጎቶቻችንን በማጣጣምና በማጠጋጋትና በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ሰጥቶ የመቀበል ባሀል ማዳበር ይጠበቅብናል።
ሌላው ነገር በሀገራዊ አንድነት ስም የግልና የቡድን ፍላጎቶችን በሌላው ላይ ለመጫን ያለ መመኮር ነው። እንደዚሁም፣ ማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በአንደኝነትና በሁለተኝነት የሚመለከተው ዜጋ ፈፅሞ መኖር የለበትም። እንደ ህዝብ የሚኖሩን ግንኝነቶች በእኩልነትና በነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ፣ መከባበርና መግባባት ያለበት መሆን አለበት። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ምን ዓይነት ታሪክ፣ ምን ዓይነት ስርዓትና ማንነት፣ ምን ዓይነት አስተዳደርና አከላለል ይኑራት በሚለው ጉዳይ ላይ የሁሉንም ፍላጎቶች ባጣጣመና በእውነታ ላይ የተመሰረተ፣ በእውቀት የተደገፈ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
ከሁሉም ነገር በላይ ደግሞ ማንም በማንም ላይ የሚጭነው ነገር መኖር የለበትም፤ ተወደደም ተጠላም ይሄ የጋራችን ቤት ነው። ከዚህ የተለየ ፍላጎት ያለው ሰው ወይም ቡድን ካለ በራሱ ክልል ወይም አከባቢ እዚያ በሚኖረው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ ማራመድ ይችላል። የአከባቢያዊነትና የሀገራዊ ፖለቲካ መደበላለቅ የለባቸውም፤ ብዙ ውዝንብር እንዲፈጠርና ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ የሆነ ፖለቲካዊ ትግል እንዲኖር የሆነው በዚሁ የአከባቢያዊነትና የሀገራዊነት ፖለቲካ መደባላቅ ነው። እዚህ ሀገር በስም ደረጃ ሀገራዊያን የሆኑ በተግባርና በአመለካከት ግን አከባቢያዊ የሆኑ ፓርቲዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። በመሆኑም የእኛ ትግልና አካሄድ ከዚህ በዓይነቱና በባህሪው የተለየ ነው መሆን ያለበት። በዚህ መንገድ የተጓዝን እንንደሆነ ብቻ ነው አዲሱን ውህድ ፓርቲ በልዩ ልዩ ባህልና ቋንቋ ያሸበረቀ ነገር ግን በፖለቲካዊ እምነት የሀሳብ አንድነት (Unity of Ideas) ባላቸው ዜጎች የተደራጀ፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የትግል መድረክ ማድረግ የምንችለው።
የውህደቱ ሁለተኛ ዓላማ የኢትዮጵያ ህዝብ በተቃዋዎች ላይ ያጣውን እምነት እንዲመለስና ለለውጥ እንዲነሳሳ ማድርግ ነው። ህዝቡ በተደጋጋሚ በፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች የተከዳ፤ በፓርቲዎች ውስጥ የሚያየው ሽኩቻና መከፋፋል እጅግ በጣም ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረጉት በመሆኑ ይህን ቁስል እንዲሽር ለማድረግና ህዝቡን ለመካስ ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ ሊገኝ አይችልም። በእርግጥ በሀገራችን ያሉት ፖለቲካዊ ችግሮች የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ብቻ ነው ማለት ባይቻልም ፓርቲዎቹ የአንበሳውን ድርሻ ስለሚወስዱ ነው። እንደ ህዝብ በፖለቲካዊ አመለካካት በኃይናማኖትና በቋንቋ  የተለያየ እንደመሆኑ መጠን ወደ እንድ ሊያሰባስበው የሚችል ሀገራዊ ሀሳብ አለመገኘቱ ነው አንዱ ችግር። ስለዚህ ይሄ ውህደት አንዱ ሊያሳካው ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ይሄ የህዝቡን እምነት መመለስ ነው።
እነዚህና ሌች ዓላማዎች ይሳኩ ዘንድ ምን መደረግ አለበት በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ደግሞ  የተወሰነ ነገር ልበል፤ ከሁሉም በላይ ጠንከራ የሆነ ሁሉንም ፍላጎቶች ሊያሰባስብ የሚችል መሪ ውህዱ ፓርቲ ሊኖረው ይገባል። የሁለቱም ፓርቲዎች ውህደት የራሱ የሆነ መለያ ያለው አዲስ ፓርቲ የሚወልድ እንደመሆኑ ለዚህ አዲስ ፓርቲ በብቃትና በሁሉም ነገር የሚመጥን አዲስ መሪ ያስፈልገዋል። አለበዚያ ውህደቱ አዲስ ወይን በአሮጌ አቅማዳ እንደመቋጠር ነው የሚሆነው።
ሁለተኛው የሀሳብ ነፃነትና ዴሞክራሲያዊ ባሀል እንዲገለብት ያላሰለሰ ጥረት ማድርግ መቻል ነው።
እንግዲህ የምንከተለው ርዕዮተ ዓለም ሊበራሊዝም ነው፤ ሊበራሊዝም ደደግሞ ነፃነትነና እኩልነት በሚሉ በሁለት ወሳኝ በሆኑ የዴሞክራሲ ምሶሶዎች ላይ የቆመ ነው። ነፃነት ሲባል አንድ ሰው ህሊናው የፈቀደለን በፈለገው ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ አቋሙንና ሀሳቡን በነፃነት ያለ ምንም መግለፅ ሲችል፤ በፈለገው ጉዳይ ላይ አቋም መያዝና የመሰለውን ሀሳብ ማራመድ ሲችል ነው። በምንም ዓይነት ሁኔታ ፍረጃ፣ ዘረኝነትና አሉባልታ የሊበራሊዝም መገለጫዎች ሊሆኑ አይችሉም። ሊበራሊዝም ራሳቸውን የቻሉ የሚተነተኑ እሴቶች ያሉት እንጂ እንደ ደብተራ ድጋም የማይታወቅ፣ የማይዘረዘርና የማይግባ ሚስጥር አይደለም። በተለይ ከፍረጃ ፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ ለመላቀቅ የውህዱና የአዲሱ ፓርቲ አመራርና አባላት ቁርጠኛ የሆነ አቋም መውሰድ የሚጠበቅባቸው ነው።
ሌላው ደግሞ በአባላት መሀል የስልጣንና የመዋቅር ግንኙነት እንጂ የጌታና የሎሌ ግንኙነት መኖር የለበትም። እዚህ የሚመጣ ሁሉ በፓርቲው አላማና ፕሮግራም እንዲሁም ህገ ደንብ ምክንያት የመጣ፣ ለትግሉ ዓላማ ወዶና ፈቅዶ የተሰባሰበ እንጂ የእገሌ ቡድን ወይም የእገሌ አጋፋሪ ሆኖ የመጣ ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ካለ ሎሌ ሆኖ የተሻለ ወደ ሚያገኝበት ቦታ ነው መሄድ ያለበት፤ ለምን በከንቱ ጊዜው ያጠፋል፤ ለምንስ በሁለት ይጎዳል ወይ ካላማው ወይ ከስጋ ካልሆነ! በዚህ ሀገር ትክክለኛ የሆነ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ከኋላቀርና ከባህላዊ አመራር ለአንዴና ለመጨራሻ ጊዜ መቆራረጥ መቻል አለብን፤  አለበዚያ ልናመጣው እያሰብነው ያለው ፓርቲያዊ አሰራር ስኬታማ ላይሆን ይችላል።
አሉዋልታ፣ ሴረኝነት፣ የጀርባ  ስም አጥፊነት ፖለቲካ አይደለም፤ ርዕዮተ ዓለማችን ሊበራሊዘም ነው፤ ግልጽ መሆን፣ በሀሳብ ተከባብሮ መነጋገር፣ በሀሳብ ተለያይቶም መከባበር ማለት ነው። በእርግጥ በሀሳብ ለመከራከር መጀመርያ ሀሳብ ሊኖርህ ያስፈልጋል፤ “ኧረ ጎራው” በራሱ ፖለቲካ ሊሆን አይችልም! ፖለቲካዊ ውይይት ለማድረግ አሳማኝ የሆነ ሀሳብ መያዝ ያስፈልጋል፤ ነፃ ህሊና ያለው ሰው ሁሉ ሊቀበለውና ሊያምንበት የሚችል ማለት ነው።
እንደዚሁም ሰርጎ ገብነት፣ አስመሳይነትና አላማ የለሽነት መዋጋት፤ እስከመጨረሻ ድረስ ሄዶ ማስወገድ አስፈላጊ ነው። የሰርጎ ገብ ሰው መለያ ምንድነው ካለን ስራ ላይ አይገኝም ወሬ፣ ጥርጣሬ በፓርቲ ውስጥ እንዲነግስ ግን ጠንክሮ ይሰራል። ዋና አለማው በአባላት መሀል ጥርጣሬና ያለመተማመን መፍጠር ነው። ለዚህ መድሀኒቱ ደግሞ ማንኛውም ፓርቲ የሚመለከት ወሬ ወይም ሀሜት የሚያመጣል ሰው ከየት አገኘኸው? ማን ነገረህ? ብለን ማጣራትና ፊት ለፊት መግጠም ያስፈልጋል። አለበዚያ እንደ ብል ነው ፓርቲው ውስጥ ለውስጥ በሚብሰከሰክ ወሬና አሉዋለታ የሚፈርሰው። እንዲህ የሚያደርግ ሰው ገዥው ፓርቲ ባይከው እንኳ ሰርጎ ገብ ከመሆን አያመልጥም። ማንም ይላከው ማን በአፍራሽ እንቅስቀሴ ውስጥ እስከተገኘ ድረስ እርሱ ሰርጎ ገብ ነው ሊባል የሚችለው።
በመጨረሻ የምለው ነገር ቢኖር አዲስ ፖለቲካዊ ባህል፣ በመከባበር ላይ የመሰረተ ፖለቲካዊ አሰራር ነው መትከል ያለብን። ከአሁን በፊት ከነበሩ ውህደቶችና ቅንጅቶች ውድቀትና ስኬት ተምረን የተሻለ ተቋማዊ አሰራር መፍጠር  አለብን። በተለይ ደግሞ ከሁሉም ነገር በላይ ከግለሰቦች ፍላጎትና ተፅዕኖ ገለልተኛ የሆነ፣ አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን ለማጥቃት የማያስችል ፓርቲያዊ ስርዓት መፍጠር ያስፈልገናል፤ በዚህ መንገድ የተጓዝን ከሆነ  ብቻ ነው ውህደቱ ዘላቂና ውጤታማ ሊሆን የሚችለው።      




የሕዳሴ አብዮት ለፖለቲካው
                                                             
                                                             አስራት አብርሃም
             
ወዳጄ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የህዳሴው አብዮት አይቀሬ እርግጠኛ ሆኗል፤ እኔም ያለኝ ግምት ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም የዛሬው ፅሁፌ የሚያተኩረው የህዳሴው አብዮት እንዴትና የት ይጀምር? በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይሆናል። በእኔ እምነት የህዳሴው አብዮት መጀመር ያለበት ከራሱ ከተቃውሞ ጎራ ነው የሚል ነው። ምክንያቱም የለውጡን ሀይል የሚመራው ይሄ የተቃውሞ ጎራ ስለሚሆን በመጀመርያ ውስጡን ማጥራትና ማጠናከር ስላለበት ነው። ስለዚህ፣ ከሁሉም ነገር በፊት የተቃውሞ ጎራው በትክክልና በተገቢው ሁኔታ እንዲታደስና እንዲለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው። ስለፖለቲካው መታደስና መለወጥ ሲታሰብ ደግሞ እንዴት ነው የሚታደሰው? እንዴት ነው የሚለወጠው? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ይሆናል። የመጀመርያው ነገር፣ እስካሁን ከተጓዝንበት ኋላቀርና ውጤት አልባ የትግል ስልት የሚያወጣን፣ የተለየ ያካሄድ ለውጥና የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ለማደረግ የሚያስችለን ብቁ የሆነ ፖለቲካዊ አመራር ወደፊት እንዲመጣ ማድረግ ነው። በተለይ ደግሞ ፖለቲካዊ ትግሉ በአስራር፣ በአደረጃጀት፣ በዴሞክራሲያዊ ባህልና በበሳል አመራር ማጠናከርና ማነፅ ቀዳሚው ተግባር ነው የሚሆነው።  
በቅርቡ ሊካሄድ ታስቦ የነበረውና በኋላ በምርጫ ቦርድ ምክንያት ለጊዜው የተቋረጠው የአንድነትና የመኢአድ ውህድ ፓርቲ ፕሬዝደንት የሚሆን ሰው ለመምረጥ በአንድነት ውስጥ የታየው እጅግ ማራኪና አስተማሪ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ውድድር፣ የሰለጠነ የእጩዎቹ ደጋፊዎች ቅስቃሳ የዚሁ የህዳሴው አብዮት ጅማሮ አድርጌ ነው የምወስደው። ይሄ ዴሞክራሲዊ የሆነ ውድድር በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ በጋዜጦችና በመፅሔቶች በጉልህ ይታይ ስለነበር የተቃውሞ ጎራ አባላት፤ ህዝቡ፣ የገዥው ፓርቲ ሰዎችም ጭምር በአንክሮ እንዲከታተሉት ምክንያት ሆኗል። ይህ እንቅስቃሴ አንድነትን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚወስደው ከሆኑም ባሻገር ልክ እንደ ዐረቡ አብዮት ወደ ሁሉም የተቃውሞ ጎራ የሚዛመት አዲስ መንፈስ ነው ብዬ ነው የማስበው። ምንም እንኳ በተወሰነ መልኩ በዴሞክራሲያዊ ውድድርና በውስጣዊ መከፋፋል መካከል ያለውን ልዩነቱ በትክክል ያልገባቸው ወይም እንዲገባቸው ያልፈለጉ አንዳንድ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር የነበረ ቢሆንም በአጠቃላዩ እንቅስቃሴ ሲታይ ግን በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ በአዲስነቱ፣ በፈር ቀዳጅነቱና በአንፀባራቂነቱ ሊታወስ የሚችል ነው። ከዚህ ልምድ በመውሰድ የአንድነት አባላት ዴሞክራሲያዊ በሆነና በሰለጠነ መንገድ መሪዎቻቸውን መምረጥ የሚችሉበት ሁኔታ ከፈጠሩ፤ የሌሎች ፓርቲ አመራር አባላትም በተመሳሳይ መንገድ መሄድ የማይችሉበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ስለዚህ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የተሳካ የተሀድሶ አብዮት ማካሄድ ከቻልን ቀጥሎ በመኢአድ፣ በመድረክ፣ በአረና፣ በኦፌኮ፣ በደቡብ ህብረት፣ በኢዴፓና በአጠቃላይ በተቃውሞ ጎራ ባሉ ኃይሎች ሁሉ ይሄ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲቀጣጠል እድል የሚፈጥር ነው የሚሆነው። በመሆኑም ውህደቱ ለጊዜው ቢጨናገፍም በአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ የተጀመረውን የትግል መነሳሳት መቀዝቀዝ የለበትም። ይሄ መነሳሳት ፓርቲውን በአዲስ መንፈስና በአዲስ ፖለቲካዊ አካሄድ ለማስኬድ በሚያስችል መልኩ ልንጠቀምበት እንችላለን። ባለበንት እንድንረግጥ ከሚያደርገን ያረጀና ያፈጀ ፖለቲካዊ አሰራር ፖለቲካው ይላቀቅ ዘንድ የለውጥ ኃይሉ በአንድነት ውስጥ የፓርቲው ህግና ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት የተሀድሶ እና የለውጥ እንቅስቃሴ ማካሄድ መቻል አለበት። ይሄ የለውጥ እንቅስቃሴ የፓርቲውን አንድነትና ጥንካሬ አስጠብቆ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ ከሆነ በሁሉም የተቃውሞ ጎራ ውስጥ የሚቀጣጠል፤ በእንቅልፍና በድንዛዜ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ሁሉ የለውጥና የፀደይ አብዮት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆን ነው።
ይሄ ብቻ አይደለም፤ እውነተኛ የተቃውሞ ኃይሉ ወደ አንድ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አውራ ፓርቲነት የሚለወጥበት ሁኔታ እንዲፈጠርም ምክንያት ይሆናል። በሁሉም ፓርቲዎች ያለው የየራስ ፓርቲ ጥግ አስይዞ ፖለቲካውን ባለበት እንዲረግጥ እያረገ ያለው ፖለቲካዊ አሰራርና ኋላቀር አካሄድ መለወጥና ከስሩ መንቀል ከተቻለ፤ የአንድ አውራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ውልደት እውን የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ከዚያ በኋላ አንድነት፣ መኢአድ፣ ሰማያዊ፣ ኦፌኮ፣ አረና ወዘተ የሚል ሳይሆን አንድ የተጠናከረ የተቃውሞ ጎራ መንፈስ ብቻ ነው የሚኖረው። ትግሉም በአምባገነኑ ገዥው ፓርቲ እና በዴሞክራሲያዊው አውራ ፓርቲ መካከል ብቻ ስለሚሆን በሰላማዊ ትግል ህዝባዊ ማዕበልና ንቅናቄ ለመፍጠር የተመቻቸ ነው የሚሆነው። የህዳሴው አብዮት በተቃውሞ ጎራ መካሄድ አለበት ሲባል፤ የተቃውሞ ጎራው በውህደትም ይሁን በሌላ መንገድ (ከየፓርቲው እየፈረሰ የተሻለ ወደ ሚለው ፓርቲ በመግባት) ወደ አንድ የለውጥ ኃይልነት ይሰባሰባል፤ ይደራጃል። ከዚያ ኋላ በጠቅላላ በሀገሪቱ የህዳሴ አብዮት እንዲካሄድና እውን እንዲሆን ማደርግ የሚከብድ አይሆንም። እንዲህ በተበታተነ ሁኔታ ከተገባ ግን መጨረሻው ያው እንደተለመደው ውድቀት ነው የሚሆነው ነው።
የተቃውሞ ፖለቲካ የለውጥ እና የመነሳሳት ሰፈር፣ የአዲስ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ መንፈስ ጎራ መሆን አለበት እንጂ በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች የከሰሩና የከሸፉ ፖለቲከኞች ማጠራቀሚያና መደበቂያ ዋሻ መሆን የለበትም። በራስ ውስጥ የህዳሴ አብዮት ማካሄድ ወሳኝ ቅድመ ሁነት የሚሆነው፣ በፖለቲካው ጎራ እየተስተዋለ ያለው አባታዊነት፣ ቡድናዊነትና ራዕይ አልባነት ይቀየር ዘንድ ነው። ለዚህ ደግሞ በመጀመርያ የፓርቲ አባላት በፓርቲያቸው ውስጥ ያላቸው መብት እኩል መሆኑ፤ ከየትኛውም የፓርቲያቸው አባልና አመራር ጋር የሚኖራቸው ማንኛውም ዓይነት ግንኙነትም በእኩልነትና በነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ታውቆና ተረጋግጦ ኋላቀርና ፊውዳላዊ ከሆነው የጌታና የሎሌ ዓይነት ግንኙነት ነፃ መውጣት አለባቸው። ከዚህም ባሻገር ፖለቲካ ማለት የአንድን ግለሰብ ወይም የተወሰነ ቡድን ምንዝር ሆኖ መኖር አድርገው የሚያስቡ አባላት ካሉ በተገቢው ሁኔታ ማሰልጠንና ማስተማር ያስፈልጋል። በተቋውሞ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የዴሞክራሲ እና የሌበራሊዝም ባህል ጠንቅቆ ያለማወቅ፤ በአጠቃላይ ደግሞ  የፖለቲካ እውቀት ማነስ ነው። ስለዚህ ይሄ ሁኔታ መቀየር አለበት፤ ይሄ የሚቀየረው ደግሞ ለአባላትና ለደጋፊዎች ተደጋጋሚ የሆነ ስልጠና መስጠት፤ የክርክርና የውይይት መድረኮች በማዘጋጀች ተመሳሳይና ተቀራራቢ የሆነ ፖለቲካዊ አቅምና ራዕይ መፍጠር ሲቻል ነው። ከዚህም በተጨማሪ በተቻለ አቅም የጥናትና የንባብ ማዕከላት በማቋቋም በፅንሰ ሀሳብ እና በፖለቲካዊ እውቀት የታነፁ ጠንካራ አባላትና ደጋፊዎች እንዲኖሩ በማድረግ ፖለቲካዊ ትግሉ በብቃትና በጥበብ ለመምራት የሚያስችል አቅምና ሁኔታ መፍጠር ይቻላል።
አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የፓርቲ ፖለቲካ ብቻውን ብዙም አዋጪ አይደለም፤ ትግሉ ወደ ህዝባዊ ማዕበልና ንቅናቄ መቀየር ካለበት ሰፋ ያለ መዋቅር መፍጠር ያስፈልጋል። ይሄ ህዝባዊ ማዕበልና ንቅናቄ ደግሞ አሁን ባሉት ድኩማን ፓርቲዎች ሊመራ የሚችል ነገር አይደለም። ሲጀመር በየፓርቲዎቹ ያሉት መሪዎች ከፍተኛ የግል የስልጣን ጥም ያለባቸውና በደመነ ነፍስ ፖለቲካውን መምራት የሚፈልጉ፤ ራዕይ አልባ መሪዎች ናቸው። በመሆኑም አሁን ልናካሄደው እያሰብነው ያለውን ፍፁም ሰላማዊ የሆነ፣ ዘመናዊ የለውጥና የህዳሴ እንቅስቃሴ ለመምራት አቅም አላቸው ተብሎ የሚታሰብ አይደለም። እኔ በበኩሌ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ በዶ/ር መራራ ጉዲና፣ በኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው እና በመሳሰሉት የስልሳው ትውልድ ቅሪቶች ትግሉ ተመርቶ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም። ሰላማዊ ትግሉ ለውጥ እንዲያመጣ ከፈለግን ፖለቲካው ላለንበት ዘመን በሚመጥኑ ጠንካራና ቆራጥ ሰዎች መመራት አለበት። የአንዷለም አራጌ፣ የናትናኤል መኮነን፣ የሀብታሙ አያሌው፤ የዳንኤል ሽበሺ ፓርቲ ከፖለቲካዊ እስር ይቅርታ ጠይቆ በተፈታ ሰው ሊመራ የሚችለው እንዴት ነው! አንዷለም አራጌ ከስርዓቱ ጋር ተደራድሮ፣ ይቅርታ ጠይቆ መውጣት፣ ከዚያም ሊቀመንበር መሆን አቅቶት እኮ አይደለም! ዳገቱ ላይ የሚቆም ሰው በመጥፋቱ እኔ እስኪ መስዋዕት ሆኜ ምሳሌ ልሆን ብሎ ነው፤ በእስር ቤት መከራና ግፍ እየተቀበለ ያለው። ለእነዚህ ጀግኖች እያስተላለፍነው ያለው መልዕክት እኮ ትክክል አይደለም። በግፍ ያሰራቸውን ሰርዓት ይቅርታ ጠይቀው እንዲወጡ የሚያደርግ ነው። ለዚህ ነው ለመታሰርና ለመሞት የተዘጋጁ አባላት በተመሳሳይ ሁኔታ ለመታሰርና ለመሞት በተዘጋጀ መሪ መመራት አለባቸው የምለው።
እኔ ለኢንጂነር ግዛቸው እንደመሪዬም፣ እንደ አንድ የሀገሬ አንጋፋ ፖለቲከኛም ትልቅ አክብሮት ነው ያለኝ፤ ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና ለዶ/ር መራራ ጉዲናም እንዲሁ ተመሳሳይ የሆነ አክብሮት አለኝ። በጊዚያቸው ያደረጉት ተጋድሎም ቢሆን እጅግ የሚመሰገን ነው። በተለይ ዶ/ር መራራ ጉዲና በኦሮሞ ህዝብ ፖለቲካዊ ትግል ላይ የራሳቸው አሻራ ያኖሩና በዓይነቱ የተለየ የትግል መንገድ ያሳዩ ትልቅ ሰው ናቸው። ለዚህ አበርክቷቸው ትልቅ ምስጋና ሊሰጣቸው የሚገባ ነው። ነገር ግን እነዚህ አንጋፋ የፖለቲካ መሪዎች ባለፉት ሀያ አመታት ትግሉን መርተው የሚፈለገው ያህል አመርቂ ለውጥ አላመጡም በሚለው መሰረታዊ ነገር ላይ ማትኮር ያሻል።
 ስለዚህ ከእኛ ወዲያ ላሰር ከሚል የግል ስሜትና ፍላጎት ወጥተው እስኪ ደግሞ ከታች ያሉት አዳዲስ ትውልዶች ይምሩትና እንየው፤ እኛ ደግሞ አጠገባቸው ሆነን ምክርና ድጋፍ እንስጥ ወደሚል በጎ ሀሳብ መምጣት መቻለ አለባቸው። በእውነቱ እንነጋገር ከተባለ፣ ኢንጂነር ግዛቸው በጣም ትልቅ ሥራ ሰሩ የሚባለው ተመልሰው ወደ መሪነት ሲመጡ ካቢኒያቸው ብቃት ባላቸው ታጋዮችና ምሁራን እንዲዋቀር ማድረጋቸው ነው። ተክሌ በቀለ፣ በላይ ፍቃዱ፣ ስዩም መንገሻ፣ ዳንኤል ተፈራ፣ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ፣ ሰሎሞን ስዩም፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳዊት አስራደ፣ ዘካርያስ የማነ ብርሃን፣ አለነ ማህፀንቱንና ሌሎችም ያየን እንደሆነ ሥራቸውን ለማመስገን እንገደዳለን። በእድሜም ቢሆን በወጣትነት እድሜ ላይ ካሉት ጀምሮ እስከ ጎልማሳ እድሜ ድረስ ያሉ ናቸው። ይሄ በራሱ ፈር ቀዳች የሚባል ዓይነት ነው። ችግሩ ግን እንዲህ ዓይነቱ ጠንካራ ስብስብ የያዘ ካቢኔ ለራሳቸው ለኢንጂነሩም ቢሆን ፈታኝ የመሆኑ ነገር ነው። እንዲህ ያለ በልምድ፣ በትምህርትና በእውቀት የተጠናከረ ካቤኔ መሪ መሆን ባንድ በእኩል መታደል ሲሆን፣ በሌላ በእኩል የግል ስሜትና የክብር ጉዳይ የሚቀድም ከሆነ ደግሞ የዚያው ያህል ስራዎች እንዲበላሹ፣ አብሮ የመስራትና የመተጋገዙ መንፈስ እንዲዳከም ምክንያት ይሆናል።
በመሰረቱ ለውጥ የምንፈልገው በፖለቲካው ዘገምተኝነት እጅግ በጣም ስለተሰላቸን ነው። ለውጥ እንፈልጋለን፤ ፖለቲካው ከገባበት የአዙሪት ሽንፈት የሚላቀቅበት መንገድ እንፈልጋለን፤ ስለዚህ እነዚህ አንጋፋ ፖለቲከኞች እንቅፋት መሆን የለባቸውም፤ ወይም ራሳቸውን ለመለወጥና በተገቢው ሁኔታ ትግሉን ለመምራት ቆርጠው መነሳት አለባቸው፤ ወይም አቅሙ ላላቸው ማስተላለፍ መቻል አለባቸው። ካሁን በፊት እንዳልኩት የፖለቲካ ብቃት በእድሜ ማነስም ሆነ መብዛት የሚገናኝ አይደለም። ችግሩ ያለው የቀደመው ትውልድ ትንታጉና ብቃት የነበረው ሁሉ በልዩ ልዩ መንገድ ማለቁ ነው። አሁን የዚያ ትውልድ አመዱ ብቻ ነው የቀረው ማለት ይቻላል፤ ያሉትም ቢሆኑ በእድሜ መግፋት፣ በኑሮ ጫና እንዲሁም በዴሞክራሲያዊ ባህል እጥረት ምክንያት አሁን ያለውን ትግል ለመምራት ይቸገራሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ። ስለዚህ ፖለቲካዊ ፍላጎትና መሪ የመሆን ምኞት ካላቸው፤ ቢያንስ በዴሞክራሲያዊና በሰለጠነ መንገድ የምናደርገውን የለውጥ ትግል እነርሱም በተመሳሳይ ሁኔታ በሰለጠነ መንገድ መታገልና መወዳደር ይችላሉ፤ በፖለቲካው መስክ እስካሉ ድረስ መብታቸውም ነው። ነገር ግን ኋላ ቀር ከሆነው የጠልፎ መጣል ሴራ እና የፍረጃ ፖለቲካ መውጣት መቻል አለባቸው።
ከሁሉም ነገር በፊት ለሀገርና ለህዝብ ነው መታሰብ ያለበት። በፖለቲካው ትግል መስክ ያገናኘንም ዋነኛው ምክንያት ይሄ የሀገር እና ህዝብ ጉዳይ ነው። የህዳሴው አብዮት ማካሄድ አስፈላጊ የሚሆነው የተወሰነ ቡድን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማርካት ሳይሆን በጠቅላላ ሀገርና ህዝብ ለመለወጥ፤ የህግ የበላይነት የሰፈነበት የተደላደለ ህገመንግስታዊ ስርዓት ለማምጣት ነው።
በሌላ መልኩ ካየነው ደግሞ፣ የተቃውሞ ጎራው የተሳካ ተሀድሶ ማካሄድ ከቻለ፣ በገዥው ፓርቲ ቤት ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን የሚችል ነው። ከዚህም ባሻገር ትልቅ የሆነ የአስተሳሰብና የአተያይ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርግ ነው። ከድል በኋላ ግንባሩን የተቀላቃሉ ወጣቶችና ምሁራን “እኛስ ከማን እናንሳለን? ለምን እውነተኛ የሆነ የተሀድሶና ለውጥ እንቅስቃሴ አናደርግም?” ብለው እንዲያስቡና እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይሄ ከሆነ ደግሞ ብዙ ነገር ተቃለለ ማለት ነው። ታንክና መድፍ እያንጋጋ ከመጣው አሮጌ አመራር ይልቅ በብዙ መልኩ እኛ የሚመስሉትን አዲሶቹ የኢህአዴግ ትውልዶች ጋር መነጋገርና መግባባት የሚቻል ነው የሚመስለኝ። ሲጀመር እነርሱ ስልጣን ቢያጡም እንዲህ እንሆናለን፣ እንታሰራለን፣ ይበቀሉናል የሚሉበት ሁኔታ የለም። ስልጣን ቢያጡ እንኳ ሰርተው ወይም ነግደው የሚኖሩበት ሁኔታ ነው የሚኖረው። እንዲያውም በስርዓቱ አማካይነት የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅምና የትምህርት እድል እንዲኖራቸው የተደረገ በመሆኑ እውነተኛና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የነፃ ገበያ ስርዓት ሲሰፍን በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ ለመሆን ከሌላው የተሻለና የተደራጀ አቅም ያላቸው ይሆናሉ።
 ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ ገለልተኛ የሆኑ ተቅዋማትና የህግ የበላይነት የሰፈነበት የተደላደለ ስርዓት እስካለ ድረስ ሰዎች በነበራቸው ፖለቲካዊ አመለካከት የሚጠቁበት ሁኔታ ፈፅሞ አይኖርም። ለዚህ ነው፤ እኔ የተሻለ አስተሳሰብና ፖለቲካዊ ባሀል በማምጣት በገዥው ፓርቲ ጥላ ስር ያሉትን ዜጎች ሳይቀር አዎንታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር የዚህ የህዳሴው አብዮት አካል እንዲሆኑ ማድረግ እንችላለን የምለው። በመሆኑም ይሄ የለውጥ ፕሮጀክትና የተሀድሶ እንቅስቃሴ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይና የሚታለፍ መሆን የለበትም። በዚህች ሀገር ያለው ፖለቲካዊ ባህል እንዲለውጥ የምንፈልግ ሁሉ ሀሳቡ ማስፋት ማጠናከር ብሎም ወደ መሬት በማውረድ ለተግባራዊነቱ ቆርጠን መነሳት፣ በተገቢው ሁኔታም መንቀሳቀስ መቻል አለብን። በዚህ መንገድ ከታገልን ለሁላችንም የምትበቃ፤ የተሻለችና ሁሉም ዜጎቿ ያለልዩነት የሚኮሩባት ሀገር እንድትኖረን ማድረግ እንችላለን። ስለዚህ የህዳሴው አብዮት በዚህ ሁኔታና እይታ ነው መቃኘት ያለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ።